የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የአርነት ትግልና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መፋፋም አርዓያ የሆነ ድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የአርነት ትግልና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መፋፋም አርዓያ የሆነ ድል ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የአርነት ትግልና የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፋፋም አርዓያ የሆነ ድል መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ገለጹ።
129ኛ የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመከበር ላይ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ድሉን በሚመለከት ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው የዓድዋ ድል የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ጦርነት እና ድል ነው ብለዋል።
የድሉ ሚስጥር ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ያሳዩት ፍጹም አንድነትና ሕብረት መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበረና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን ያጎናጸፈ ድል እንደሆነም ገልጸዋል።
ለአፍሪካውያን የአርነት ትግልና የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ መፋፋም አርዓያ የሆነ ድል ነውም ብለዋል።
የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች የእኩልነት ጥያቄ እንደ ፋና ዋጊ የሚወሰድ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ትውልዱ የዓድዋ ድል እንዲሁ የተገኘ ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት፣ የአንድነት ውጤት መሆኑን መማር እንደሚገባውም ገልጸዋል።
ለጠላት ተላላኪ ባንዳ አለመሆንን ከዓድዋ ድል ጀግኖች መውረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሀገር ክብር መስጠትን ከድሉ መማር እንደሚገባ ገልጸው ለሰንደቅ ዓላማ፣ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለህገ መንግሥት እና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር መሥራትና ማክበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።