የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችን የይቻላል አስተሳሰብ ያሰረፀ ነው- ሙሳ ፋቂ ማህማት - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችን የይቻላል አስተሳሰብ ያሰረፀ ነው- ሙሳ ፋቂ ማህማት

አዲስ አበባ፤የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፦የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችን የይቻላል አስተሳሰብ ያሰረፀ ነው ሲሉ የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ገለጹ።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ጦርነትን የማሸነፍ ታሪክ ብቻ አይደለም ብለዋል።
የዓድዋ ድል ጦርነትን የማሸነፍ ታሪክ ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ለመላ ጥቁር ህዝቦች የይቻላል አስተሳሰብን ያሰረፀ ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል በአንድነትና ትብብር የአፍሪካን መፃኢ ዕድል የተሻለ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
አፍሪካ ለደረሰባት በደል ካሳ የምትጠይቅበት ዓመት እንደመሆኑ በዓሉ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።
አፍሪካውያን ከተባበሩና በአንድነት ከቆሙ ይሳካ የማይመስሉ ድሎችን ማስመዝገብና የተሻለ አህጉር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲልና የአፍሪካውያን ተምሳሌት መሆኗንም በቅርቡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉ የልማት ስራዎች ምስክር ናቸው ብለዋል።