ቀጥታ፡

የኦሜድላ ስፖርት ክለብን ወደ ቀደመ ገናና ስሙ ለመመለስ በትኩረት ይሰራል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ የኦሜድላ ስፖርት ክለብን ወደ ቀደመ ገናና ስሙ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

19ኛው ሀገር አቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል "በላቀ የስፖርት ተሳትፎ ብቁ እና ንቁ የፖሊስ ሠራዊት እንገነባለን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ ውለታ ከዋሉት አንዱ የኦሜድላ ስፖርት ክለብ መሆኑን አስታውሰዋል።

በአትሌቲክስ ዘርፉም ጀግናው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ኮማንደር ጌጤ ዋሜ ፣ በላይነህ ዲንሳሞን የመሳሰሉ ስመጥር አትሌቶችን ያፈራ ክለብ እንደሆነ አስታውሰዋል።

የኦሜድላ ስፖርት ክለብን ወደ ቀደመ ገናና ስሙ ለመመለስና በቀጣይ በኢትዮጵያ በሚደረገው አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው መንግስት ስፖርት ለሀገር ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከተሰጠው ሕግን የማስከበር ኃላፊነት ጎን ለጎን በስፖርቱ ዘርፍም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ በተደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የእግር ኳስ ቡድን የሶማሌ ክልል የእግር ኳስ ቡድንን 1 ለ 0 ማሸነፉን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም