በ30 ደቂቃዎች ሽልብታ ያለፉ 48 ሰዓታት - ኢዜአ አማርኛ
በ30 ደቂቃዎች ሽልብታ ያለፉ 48 ሰዓታት

የብዙሃኑ ቀለሜ ተማሪዎች ሕልም ነው- ሃኪም መሆን።
በአካባቢ ማህበረሰቡ ዘንድም ቢሆን ብዙን ጊዜ ጎበዝ ተማሪ ዕድል ፈንታው 'ዱክትርና' ተደርጎ ይሳላል።
እናም ኤልሳቤጥ ግና ከለጋነቷ ጀምሮ የቀለሜነት ጉዞዋ የተመለከቱ በዙሪያዋ የተኮለኮሉ ወዳጅ ዘመዶች 'ሃኪምነት' ተመኙላት።
ከቅድመ መካነ-አዕምሮ የትምህርት ሕይወቷ 'ዶክተር ትሆኛለች' አሏት።
እርሷም ተመኘች፤ ራዕይ ሰነቀች።
ለምኞቷ ስኬትም ጊዜና ሁኔታን አዋደደች። ቀለሜነቷን በማንበብ ዋጀች።
በትናንት ትኩረት የዛሬዋን ጡብ ደረደረች፤ የነገ መሻቷን ሰራች።
በአላውቅም ስሜት ለማወቅ ጣረች፤ ለሌሎች አርዓያ ሆና ቀጠለች-ኤልሳቤጥ አርዓያ።
እነሆነ ዛሬ ሕልሟን ጨበጠች፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤት 3 ነጥብ 93 ውጤት ይዛ ተመረቀች።
ዝም ብሎ መመረቅ ብቻ ግን አይደለም፤ ቀለሜዋ ኤልሳቤጥ የዩኒቨርሲቲውን የዓመቱን የወርቅ ሜዳሊያ ወሰደች።
የትናንት የሃኪም ባለራዕይዋ፤ የዛሬዋ የጠቅላላ ሃኪምነት ምሩቋ ዶክተር ኤልሳቤጥ አርዓያ 'ሕክምና ባልገባ ኖሮ ምን እሆን ነበር' ብላ ትጠይቃለች።
በምትወደው ሙያ ተምሮ ለመመረቅ፤ ላለፈችበት ውጣ ውረድ ቤተሰብ የነበራቸው ውለታ በኤልሳቤጥ አንደበት ቃላት ያንሳሉ።
በሕክምና ትምህርት ቤት (ለዚያውም ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ለመመረቅ) የቀለሜ ነት ዳራ መያዝ ብቻውን በቂ አይደለም።
ቀልብ፣ ጊዜና ትኩረትን በቅጡ መጣጣም እንዳለበት ትናገራለች።
እንደ አለመታደል ሆኖ በኤልሳቤጥና የዘመነ-ትምህርት ጓዶቿ ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽን ተከስቷል።
ይህም ከሰባት ዓመታት ወራት ጉዳይ የሆነው የትምህርት ዘመናቸው ወደ ስምንት ዓመታት እንዲገፋ ምክንያት ሆነ።
ሆኖም የስምንት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በሥነ ምግባርና በዕውቀት ጎልብተው ከመመረቅ አላገደንም ትላለች።
በተግባር ተኮር ትምህርት ቆይታዋ በተለይም ሕፃናት ታካሚ ስትመለከት ከፉኛ እንደፈተናት የምትገልፀው ኤልሳቤጥ፤ ይህ ግን ብርቱና ጠንካራ ማንነት ለመገንባት አስችሏታል።
ሕክምና ትምህርት ምን ያህል ዕለታዊ የጥናት ዝግጅት የሚጠይቅ ከባድ ትምህርት ዘርፍ እንደሆነ ኤልሳቤጥና ጓደኞቿ ምስክር ናችው።
በተለይም የመጨረሻዎቹ ዓመታት በጊዜ ዕጦት ፈተና የታጀቡ ናቸው ትላለች።
"48 ሰዓታትን በ30 ደቂቃዎች ሽልብታ ብቻ ያሳለፍንበት ጊዜ ነበር" ትላለች ኤልሳቤጥ።
ያም ሆኖ በአስተማሪዎችም ድጋፍ፣ በተማሪዎችም ብርታት አስቸጋሪ ቀናት አልፈው፤ ኤልሳቤጥ በማዕርግ ተመረቃለች።
ከትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር በርሐኑ ነጋ እና ከጤና ሚኒስትሯ ዶከትር መቅደስ ዳባ ዕጅ ክብርና ሽልማቷን አጥልቃለች።
የብዙ ዓመታት ዕንቅልፍ ዕጦት፣ የሰርክ ጥረትና ግረት ትሩፋቷን ዛሬ ተቋድሳለች።
የትምህርትንም፤ የሕይወትንም ፈተና ተቋቁማ ድል የተቀዳጀችው ዶክተር ኤልሳቤጥ 'ሁሉንም አውቃለሁ ማለት የውድቀት መነሻ ነው' ትላለች።
አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለተሻለ ነገር ሁሌም መትጋት ይገባል ትላለች።
"ሴቶች ይችላሉ፤ ለስኬት የሚያግዳቸው ነገር የለም" የምትለው ኤልሳቤጥ፤ ምንም ጫና ቢኖር ሕልምን ለመኖር 'እችል ይሆን' ብሎ ማቅማማት እንደማያሻ ትመክራለች።
እንደ ኤልሳቤጥ ሁሉ ዕልፍ ብርቱ ቀለሜዎች ፈተናዎችን ሳይበግራቸው ወሳኙን የትምህርት ምዕራፍ ተሻግረዋል።
አካል ጉዳቱ ሳይበግረው ከነኤልሳቤጥ አርዓያ ጋር ከፍተኛ ውጤት ይዞ የተመረቀው ዶክተር ቢኒያም ኢሳያስ ለዚህ አብነት ነው።
ያለፉት ዓመታት ያለድካምና ስልቸታ ሰርክ የማጥናትና የመማር ዕለታዊ ተግባራቱ የዛሬዋን ውብ ቀን እንዳመጣችለበት ቢኒያም ይናገራል።
ከራሱ ጥረት ባሻገር በጓደኞቹ የተደረገለትን ድጋፍም አልዘነጋም።
ዘመኑ ዕድልም፤ ፈተናም እንዳመጣ የሚገልፀው ዶክተር ቢኒያም፤ ዕውቀትንና ክህሎትን በቀላሉ ማበልፀግ የሚያስችሉ ምቹ የቴክኖሎጂ አፈራሽ ዕድሎች እንዳሉ ይናገራል።
አዎ በርካቶቹ እንደ ምሩቃን ሃኪሞቹ ኤልሳቤጥና ቢኒያም ፈተናን በድል ቀይረው በአድዋ ድል መታሰቢያ ዋዜማ ተመርቀዋል፤ ድላቸውን አጣጥመዋል።
አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ቤት 53 በሕክምና ዶክትሬት፣ 21 በጥርስ ህክምና፣ 23 ደግሞ አንስቴዥያ በድምሩ 197 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።