ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠቱን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ሚና  ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት  ላይ በርካታ ተግባራት አከናውኗል፡፡

በዋነኝነትም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የመምህራን አቅም ግንባታ ተግባራት ላይ  ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለፈው ክረምት ብቻ  በሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት ለሚያስተምሩ ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑ መምህራንን ጨምሮ ለትምህርት ማህበረሰብ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ለአብነት አንስተዋል፤ ወደፊቱም  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።


 

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኝነት የመምህራን ብቃት ክፍተት እና ሌሎች ችግሮች እንደተግዳሮት እንደሚነሱ ጠቁመዋል።  

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተግባር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት  በሰጡት አስተያየት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት  ተሳትፎ የሚጠይቅ  ነው።

በቀጣይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች  የኮሌጅ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም