ቀጥታ፡

በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት የተረከብናትን ሀገር ከድህነት ለማላቀቅ ጠንክረን እንሰራለን - የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች

ጋምቤላ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት የተረከብናትን ሉአላዊት ሀገር ከድህነት ለማላቀቅ የድርሻችንን ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።

ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል በሚል መሪ ሀሳብ 129ኛው የአድዋ ድል በዓል በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጀቶች እየተከበረ ነው።

ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጀግነትና የአንድነት ተጋድሎ የታየበት ብሔራዊ ዓርማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ወጣት እየሩስሌም ፋሲል በሰጠችው አስተያየት ጀግኖች አባቶች የወራሪውን ጦር በተባበረ ክንዳቸው በአድዋ ተራራ ድል በመንሳት ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር አስረክበውናል ብላለች።

በመሆኑም በታላቅ ተጋድሎና የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ጠብቀው ከነክብሯ የተረከብናትን ሀገር ከድህነት ለማውጣት የድርሻችንን ከፍተኛ ኃላፊነት እንወጣለን ብላለች።

የአሁኑ ትውልድ በዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ያሳዩትን ህብረትና አንድነት አጠናክሮ በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማት የተረጋገጠባት ሀገር የመገንባት ድርሻ እንዳለበት የገለጸው ደግሞ ወጣት ኡጁሉ ኡባንግ ነው።

በተለይ ከቀደምት አባቶች ሀገራዊ ፍቅር፣ አንድነትና የድል አድራጊነት ወኔን በመማር በድህነት ላይ በጋራ መዝመት አለብን ብሏል ወጣት ኡጁሉ።

በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት የተረከብናትን ሉአላዊት ሀገር ከድህነት ለማወጣት ከኛ ያልተቆጠበ ጥረት ያስፈልጋል ያለው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ኡቸዶ ኡከች ነው።

የክልሉን ብሎም የሀገሪቷን ዘላቂ ሰላም በማጽናት የታለመውን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በተለይ ከወጣቱ ብዙ እንደሚጠበቅም ተናግሯል።

በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች በተከበረው የአድዋ ድል በዓል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም