የዓድዋ ድል ታሪክን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለትውልድ እናሻግራለን- ዩኒቨርሲቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ታሪክን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለትውልድ እናሻግራለን- ዩኒቨርሲቲዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዓድዋ ድልን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
ትውልዱ ሀገርና ህዝብ ሊያሻግር የሚችል ዕውቀትና ክህሎት በመታጠቅ የዓድዋን ገድል በልማት ስራዎች መድገም እንዲችል እየተሰራ መሆኑንም ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያዊያን የተቀዳጁት የዓድዋ ድል በጊዜው በጭቆና ስር ለነበሩ የመላ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጮራን የፈነጠቀና ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መነሳሳት የፈጠረ መሆኑንም ነው ታሪክ የሚዘክረው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ራሄል አርጋው (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት አርማ፣ የኢትዮጵያውያን የሁልጊዜም የታላቅነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ያስመዘገቡት ታላቅ ድል በቅኝ ግዛት ውስጥ ለነበሩ በርካታ ሀገሮች ምሳሌ ከመሆን ባለፈ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው የአሁኑ ትውልድ የዓድዋን የጽናትና የአንድነት መንፈስ እንዲላበስ ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዕውቀት በመላበስ በልማት እንዲደገም እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ድሪባ ኢቲቻ(ዶ/ር)፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለብዙ አፍሪካ አገሮች ሉዓላዊነትንና ዳር ድንበርን ለማስከበርና የአልገዛባይነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል።
አባቶቻችን የነበራቸው አንድነት፣ የዓላማ ፅናት፣ የሀገር ፍቅር ስሜትና አልገዛ ባይነት ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ሰጪ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በመዋጋት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት በሚሰሩ ስራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ታድዮስ ሜንታ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን መላ ጥቁር ህዝቦች ኩራት እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው አንድ ሆነው በመቆማቸው ዘመናዊ የጦር መሳርያ ታጥቆ የመጣውን ወራሪ ሃይል ድል ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
የአሁኑ ትውልድም እንደሀገር ድህነትን ለማሸነፍ በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም ነው የገለጹት። ዩኒቨርሲቲው ትውልዱ የዓድዋ ድል ምንነትን በአግባቡ ተረድቶ ለሀገሩ ቀጣይነት ያለው ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ እያስጨበጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የማህበረሰብን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም የዓድዋ ድልን በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በርካታ የተሰሩ ስራዎች መኖራቸው ገልፀው፤ በቀጣይም የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሀሳብ የካቲት 23 ቀን 2017 ይከበራል።