የአድዋ ድል መላው የሀገራችን ህዝቦች በአንድነት የፈፀሙት የጀግንነትና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው - ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል መላው የሀገራችን ህዝቦች በአንድነት የፈፀሙት የጀግንነትና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው - ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦የአድዋ ድል መላው የሀገራችን ህዝቦች በአንድነት የፈፀሙት የአለማችን ታላቅ የጀግንነት ታሪክና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።
አዛዡ ይህንን የገለፁት በዕዙ ጠቅላይ መምሪያ 129ኛ የአደዋ ድል በአል በተከበረበት ዕለት ነው።
በበዓሉ ላይ አዛዡ እንደገለጹት የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለ ብሔርና እምነት ልዩነት ለሀገራቸው ክብር በጋራ ቆመው በህይወታቸውና በደማቸው የፃፉት የአለማችን ታላቅ የጀግንነት ታሪክና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ ነው።
የክፍሉ አባላትም የዚህ ወደር የሌለው ታሪክ ባለ አደራ መሆናቸውን አውቀው ሀገራቸውን በፅናት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የዕዙ ፋይናንስ ስራ አመራር ሃላፊ ኮሎኔል መርጋ ቀልበስ በበኩላቸው 129ኛ የአድዋ ድል በአልን ስናከብር የተጣለብንን አደራ እያስታወስን የኢትዮጵያዊነትን የላቀ ክብር ዛሬም በመስዋዕትነታችን ጠብቀን ለማስቀጠል ዳግም ቃል በመግባት ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።