የአድዋ ድል የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ነው - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ነው - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የጋምቤላ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የሲዳማ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ባስተላለፉት መልዕክት የአድዋ ድል የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ባስተላለፉት መልዕክት የአሁኑ ትውልድ የአንድነትና የኅብረትን ኃያልነት ከአባቶቹ በመማር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ አሻራውን ሊያኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአድዋ ጦርነት ወራሪው የጣልያን ጦር ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰበት መሆኑንም አውስተው፤ ድሉ የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት እንደሆነም ገልጸዋል።
የአድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ቀኝ ገዢዎች በጥቁር ሕዝብ ተሸንፈው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ የነፃነት አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት ታሪካዊ ቀን መሆኑንም አስታውሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ዓድዋ የክብርና የኩራታችን ምንጭ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ተምሳሌትና የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ መሰረትም ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ስኬት በማስመዝገብ ዳግማዊ አድዋን የሰሩት የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በቀጣይም ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመጠበቅ በጋራ ጥረትና ትጋት የኢትዮጵያን ብልፅግና ዕውን በማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ድል እንደሚያስመዘግቡ ጽኑ ዕምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደስታ ሌዳሞም ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያዊያን ለሃገር ሉዓላዊነት የማንደራደር ታላቅና ጀግና ህዝብ መሆናችንን ለዓለም ያስመሰከርንበት ነው ብለዋል።
አባቶቻችን በአንድነትና በህብረት በአድዋ ያደረጉት ተጋድሎ የጥቁር ህዝቦችን ጀግንነት ያሳየ ነው ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ ትውልዱ ከዚህ በመማር ድህነትን በጋራ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ከፍታ ለማሻገር ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።