ዓድዋ የጀግንነታችን ጥግ፤ የኢትዮጵያዊነታችን ክብር፤ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፤ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት ነው- ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋ የጀግንነታችን ጥግ፤ የኢትዮጵያዊነታችን ክብር፤ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፤ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት ነው- ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017 (ኢዜአ)፦ ዓድዋ የጀግንነታችን ጥግ፣ የኢትዮጵያዊነታችን ክብር፤ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፤ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት በመሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ክብራችን ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የአድዋ ጦርነት መላው ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ቅንጣት ያህል የማንደራደር ታላቅና ጀግና ህዝብ መሆናችንን ለዓለም ህዝብ ያስመሰከርንበት ነው።
በአድዋ የአልደፈር ባይነታችን ወኔና ፅናታችን በተግባር የታየበት ብቻም ሳይሆን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የደመቀበት ገድል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
የአድዋ ጦርነት ሲታሰብ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያስቆጣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ለአንድ አላማ ያስተሳሰረ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያዊነትን ያሳየ የጋራ የነፃነት ትግላችን ነውም ብለዋል።
የጥቁር አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመውጣት ላደረጉት ተጋድሎ የሞራል ስንቅ የሆናቸው በአድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያውያን አንፀባራቂ ድል መሆኑንም ተናግረዋል።
በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር ህዝቦች በቆዳ ቀለማቸው የተነሳ ለደረሰባቸው የዘር መድልዎና የጭቆና ቀንበር ነፃ ለመውጣት ላደረጉት ትግል የአድዋ ድል የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንዳላበሳቸውም ገልፀዋል።
የአድዋን ድል በዓል ስናከብር ኢትዮጵያውያን የጋራ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ክብርና የድል ፋና ወጊ በመሆኑ ለአባቶቻችን ተጋድሎ ታላቅ ክብር መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
የአባቶቻችን የጋራ አንድነታቸውና ህብረታቸው በአድዋ ወረራ ላይ ባደረጉት ተጋድሎ የጥቁር ህዝቦችን ጀግንነት ያሳየ ነው ብለዋል።
ትውልዱ ከአድዋ በመማር ድህነትን በጋራ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ከፍታ ለማሻገር ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።