የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ ይመረቃል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ ይመረቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017 (ኢዜአ)፦ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ ይመረቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማዕከሉ የስብሰባ፣ የኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን ዘርፍን(MICE) ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት አንድ ተጨማሪ አቅም ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ደረጃን እንደጠበቀ ተቋምነቱ የንግድ ቱሪዝምን በማሳደግና አለም አቀፍ ኹነቶችን በመሳብ ኢትዮጵያን የስብሰባዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማዕከሉ ራዕይ መዲናዋን አዲስ አበባን በአህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ኹነቶች መስተንግዶ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆና ማየት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ታላቅ ጉዞ መጀመሩ ለመላው ኢትዮጵያውን ከፍ ያለ ኩራት ነው ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት።
ማዕከሉ ሰፊና ጥሩ ዕይታ የሚፈጥር አረንጓዴ ቅጥር ግቢና በቂ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ያለው ሲሆን ሁለት ትላልቅና 8 መካከለኛና አነስተኛ የስብሰባ አዳራሾቹም እስከ 10 ሺህ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ ይችላሉ።
ለትራንስፖርት አመቺ ሥፍራ ላይ የሚገኘው ማዕከሉ ቢሮዎችን፣ ባንኮችን፣ ሱቆችን፣ ካፌ እና ሬስቶራንቶችን የያዘ፤ 15 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የውጭ ኹነቶች ማስተናገጃ ሥፍራም መያዙ ተገልጿል።
የማዕከሉ ግንባታ መንግስት የኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ዘርፉን ለማነቃቃት ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ሲሆን የግሉም ዘርፍ የተካፈለበትና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም እንዳለውም ይታወቃል።
ትላልቅና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን እያዘጋጀች ለምትገኘው ሃገራችንም ለዘርፉ እሴት የሚጨምር ነው።