የዓድዋ ድል የቤት ስራዎች- በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የቤት ስራዎች- በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አንደበት
ኢዜአ 129ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት መልከ ብዙ ትሩፋቶች ካወረሰው የዓድዋ ድል በመማር በተሰማሩበት መስክ ለሀገር የሚበጅ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን የቤት ስራ ወስደዋል።
በኦሮሚያ ክልል የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ መካከል አራተኛ ዓመት የሕግ ተማሪዋ አሚራ ፋቲ እንደምትለው ዓድዋ የሀገር ፍቅር ስሜት የወለደው አንድነትና እና ጀግንነት ውጤት ነው።
ከቀደምት አባቶች ለሀገር በጋራ መቆምና ለሀገር ጥቅም የማስቀደም እሴት በመማር የጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ለማፍለቅ የቤት ስራ አለብን ትላለች።
በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ተማሪው ኬሩዲን መሐመድ በበኩሉ የአድዋ ድል ትልቁ ትጥቅ ጠንካራ አንድነት እንደነበር በማውሳት የዘመኑ ችግሮቻችንን ድል ለመንሳትም በአንድነት ተሰልፎ መስራት እንደሚገባ ገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ የብሩህ ተስፋ አካዳሚ ተማሪዋ አዶናዊት ህዝቅኤል፤ የመላው የጥቁር ህዝቦች ድል ከሆነው ዓድዋ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ምንጊዜም በጋራ መቆም እንዳለብን የቤት ስራ የሰጠ ነው ትላለች።
በዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ወንድይፍራው ያሳቡ በበኩሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ትዕምርት ከሆነው ዓድዋ 'በትምህርቴ ጠንክሬ በመማር የሀገሬን ስም አስጠራለሁ' ስትል የአድዋ ውርስ የቤት ስራዋን ተናግራለች።
የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታሁን ነጋሽ ለአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ የሆነው ዓድዋ ድል ሀገራዊ ጥሪና ወኔ ሰንቀው ድልና ገድል ለፈጸሙ ቀደምት አባቶች ዘንድ ትልቅ የሀገር ፍቅር አደራ እንዳወረሱ ያምናሉ።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ፤ አባቶቻችን ድል የመቀዳጀታቸው ሚስጥር የአንድነት እና የትብብር ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ በአንድነትና በመተባበር መሰለፍ የየዘመኑ ትውልድ የቤት ስራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ግድቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን ያለምንም ልዩነት በአንድ ላይ ያሰለፈ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቦንጋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አልማዝ ገበየሁ ከአድዋ ከምንማረው ቁም ነገር አንዱ ሕዳሴ ግድብ መሰል ፕሮጀክቶችን ዕውን ማድረግ ላይ መረባረብ እንደሚገባ ነው ይላሉ።
በይቻላል መንፈስ ለግድቡ ግንባታ ባደረጉት ርብርብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
አቶ ዳዊት ተካ የተባሉ የዚሁ ከተማዋ ነዋሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ያለምንም ልዩነት በአንድ ላይ ያቆመና ያሰለፈ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግድቡ ተጠናቆ ወደአገልግሎት እስኪበቃ በጽናት መደገፍም አንዱ የአድዋ የቤት ስራ መሆን እንዳለበት ነው ያነሱት።
በሀገር ክብርና ሉዓላዊነት መደራደር እንደሌለብን ከአድዋ የቤት ስራ ወስደናል የሚሉት ሌላው የቦንጋ ነዋሪና የጸጥታ ዘርፍ ባለሙያው ኢንስፔክተር ብርሃኑ አበራ ናቸው።
በመሆኑም የዛሬው ትውልድ በልማቱ ተጨማሪ ድሎችን ለማስመዝገብና ኢትዮጵያን ክፍ ለማድረግ ችግሮችን በምክክር በመፍታት በአንድነት መቆም ይኖርብናል ነው ያሉት።