የዓድዋ ድል የአርበኝነትና የጀግንነት እሴት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የአርበኝነትና የጀግንነት እሴት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል በታሪካዊነቱ አቻ ያልተገኘለት የአርበኝነት እና የጀግንነት እሴት መሆኑን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ገለጹ።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ተከብሯል።
አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የዓድዋ ድል ሉዓላዊነትን ያስከበርንበት ወራሪ ጠላትን ያሳፈርንበት የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል ነው ብለዋል።
አድዋ ድል በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩ ሀገሮች የይቻላል መንፈስ በመፍጠር የነጻነት ፋና ወጊ የሆነ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
ድሉን ስንዘክር ሀገርን ማስቀደም፣ በአንድነት ጸንቶ መቆም፣ የዓላማ ጽናት እሴቶችን መማር እንደሚገባ ገልፀው፤ የዘመኑ ትውልድ ዓድዋ ልማትን በማረጋገጥ የበለጸገች ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ነው ብለዋል።
በሪያድ የኢትዮጵያዊያን ኮሙኒቲ ሊቀ መንበር መምህር ሱለይማን ሙሃመድ በበኩላቸው ዓድዋ የዓለም ጭቁኖች በገዢዎቻቸው ላይ እንዲነሱ ያደረገ እና ለኢትዮጵያዊያንም የኩራት ምንጭ የሆነ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
129ኛው የዓድዋ ድል ቀን በዓል ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በሪያድ የኮሚኒቲ አመራር አባላት፣ ዲፕሎማቶች እና የመከላከያ አታሺዎች መገኘታቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።