ትውልዱ እንደ አድዋ ዘመቻ በሀገራዊ ልማቶች ላይ በጋራ ተሰልፎ አሻራውን ማኖር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ እንደ አድዋ ዘመቻ በሀገራዊ ልማቶች ላይ በጋራ ተሰልፎ አሻራውን ማኖር አለበት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ የዘመኑ ትውልድ እንደዓድዋ ዘመቻ በጋራ በመሰለፍ በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ እንደሚገባው ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ተመራማሪ ተፈሪ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ በነገው ዕለት ይከበራል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር እና የታሪክ ተመራማሪው ተፈሪ መኮንን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ አድዋ ኢትዮጵያዊያን የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቦታና የማንነት ልዩነት ሳያግዳቸው በጋራ ተሰልፈው ያስመዘገቡት ድል ነው።
ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ከሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አቋርጠው በደም እና አጥንት የጻፉት የአድዋ ድል ለትውልዱ የአሸናፊነት ስነ ልቦና አውርሶ ያለፈ ትውልድ ተሻጋሪው ድል ነው ብለዋል።
የዘመኑ አዲስ ትውልድም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ ተሰልፎ በማልማት የራሱን አሻራ ማኖር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ጣሊያን በ1888ዓ.ም ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ሰራዊቷን አሰልፋ ብትመጣም ዓድዋ ላይ በተካሄደ ጦርነት በኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ድል ተነስተዋል፤ ድሉም የጥቁር ህዝቦች አጻባረቂ ድል ሆኗል።