ቀጥታ፡

በሕብረት የመቆም አሻራዎች ዓድዋ ድልና ሕዳሴ ግድብ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድልና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለጋራ ጥቅምና ዓላማ በሕብረት የመቆም ውጤቶች ናቸው ሲሉ የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተባበረ ክንድ ባደረጉት ተጋድሎ የዓድዋን ታሪክ በደማቁ መጻፍ ችለዋል።

ይህ ድል በጭቆና ውስጥ ለነበሩ የመላ ጥቁር ህዝቦች ትልቅ የመነሳሳት ወኔ የፈጠረ ታሪካዊ ሁነት ሆኗል።

የአሁኑ ትውልድ ከድህነት ጋር ለሚያደርገው ተጋድሎ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በራሱ አቅም በመገንባት የዓድዋን ታሪክ መድገም መቻሉንም አንስተዋል።

የጽናትና የጥንካሬ ውጤት የሆነውና ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ የጀመሩት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክትም አሁን ላይ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለጋራ ጥቅምና ዓላማ በህብረት መቆም ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የዓድዋ ድልና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳያ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ፈተናዎችን በተባበረ ክንድ መመከት ውጤቱ ያማረ ነው መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት የድል ምልክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም