ዓድዋ ድል እና ሕዳሴ ግድብ የጀግንነትና የስኬት ማሳያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋ ድል እና ሕዳሴ ግድብ የጀግንነትና የስኬት ማሳያዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2017(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድልና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስከበሩ፣ ጀግንነትና ስኬታችንን ያሳዩ ድሎች ናቸው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ በነገው ዕለት ይከበራል።
ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ያለውን ኃይል፣ ሀብትና የአውሮፓ ሀገራትን ድጋፍ አግኝቶ ቢመጣም ዓድዋ ላይ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር ጦርነት ሽንፈት ተከናንቦ ተመልሷል።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ አንድን የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይል በአሸናፊነትና ድል አድራጊነት መክታ ዓለምን ያስደነቀችበት መሆኑንም አውስተዋል።
የጥቁር ህዝቦች ሀገርና መንግስት የነጭን ቅኝ ገዥ ኃይል ማሸነፉ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የታፈረችና የተከበረች ከማድረጉ ባለፈ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ሆኗል ነው ያሉት።
ድሉ በዓለም የዲፕሎማሲ ታሪክ ትልቅ እጥፋት መፍጠሩንም ገልጸዋል።
አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ህዝብ ጀግንነት ምሳሌ አድርገው በመታገል የቅኝ ገዥዎችን ስርዓት በመገርሰስ ነፃነታቸውን እንዳረጋገጡም ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ብቻ ሳይሆን በየጊዜያቱ ሀገራቸውን ሊወርሩ የሞከሩ ኃይሎችን ሁሉ በአንድነትና ጀግንነት በመመከት ሉዓላዊነቷን አስከብረው መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድም ልክ እንደ ዓድዋ በአንድነት ተነስቶ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ዕውን በማድረግ የራሱን ታሪክ ጽፏል ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን በራስ አቅም፣ እውቀት፣ ውሳኔና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ፕሮጀክቱን በማሳካት በዓለም ህዝብ ዘንድ የስኬት ምልክት ሆኖ እንዲታይ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷ እያደገ መምጣቱን በመጥቀስ የአፍሪካን ከፍታ በማረጋገጥ ረገድም በምሳሌነት ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ገልጸዋል።
ትውልዱ የዓድዋና የህዳሴ ግድብን ስኬት በምሳሌነት ለሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ልማት፣ የዲፕሎማሲ ከፍታ በትጋት መስራት እንዳለበትም አስረድተዋል።