ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በትምህርት ዘርፍ ባላቸው ትብብር ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ከሩሲያ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ምክትል ሚኒስትር ሞጊሌቭስኪ ኮንስታንቲን ሊች ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ለአምባሳደር ገነት የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቫለንቲና ማትቪየንኮ በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የስራ ጉብኝት ውጤቶች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

አፈ ጉባዔዋ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሁለቱን ሀገራት የትምህርት ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

ሩሲያ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት እድል አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።

አምባሳደር ገነት ሩሲያ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እየሰጠች ለምትገኘው ነጻ የትምህርት እድል ምስጋና አቅርበው የሚሰጠው እድል በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ትብብር በፍጥነት እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።

የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ እና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት የትብብሩን ከፍታ የሚያሳድግ ጠንካራ አጋርነት መፍጠር እንደሚገባ መግለጻቸውን በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም