የዝክረ ዓድዋ ድል በዓል በዶሃ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የዝክረ ዓድዋ ድል በዓል በዶሃ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፦ በቀጠር ርዕሰ መዲና ዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከቀጠር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር ጋር በመሆን የ129ኛ የአድዋ ድል በዓል በኤምባሲው ቅጥር ግቢ አክብረዋል።
በቀጠር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፌይሰል አሊይ ኢብራሂም፣ የቀጠር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አሚኑ ኑሩ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።
አምባሳደር ፌይሰል አሊይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዓድዋ የኢትዮጵያዊያን ኩራትና የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው።
የዓድዋን ድል ታላቅነት ለትውልድ ማስገንዘብና ከአባቶቻችን አንድነትና ትብብር ትምህርት ወስደን ለአገራችን ልማትና ዕድገት በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በቀጠር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አሚኑ ኑሩ በበኩላቸው፣ የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችን ምልክት ከሆነው የአድዋ ድል ታሪክ አዲሱ ትውልድ መማር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የቀጠር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝክረ ዓድዋ ድልን በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ክዋኔዎች አክብረዋል።
የዘንድሮው የአድዋ ድል ክብረ በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ ይዘከራል።