ቀጥታ፡

በዓሉ የተጀመረው የህብረ ብሄራዊ አንድነት ትርክት የበለጠ የጋራ መግባባት እንዲደረስበት አስተዋጽኦ አድርጓል

አርባምንጭ፤የካቲት 21/2017(ኢዜአ):-የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጠናከርና የተጀመረው የህብረ ብሄራዊ አንድነት ትርክት የበለጠ የጋራ መግባባት እንዲደረስበት አስተዋጽኦ ማድረጉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

19ኛው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና አሰጣጥና የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።

የዘንድሮው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት ይበልጥ እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተጀመረው የህብረ ብሔራዊ አንድነት ትርክት የተሻለ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስበት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያድርግ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓሉ የአገሪቱን ገጽታ በመገንባት ከፍታዋን ያረጋገጠ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አፈ ጉባኤ ሰአዳ አብዱራህማን ናቸው።

በዓሉ ከበዓልነት ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ህዝቡ መንግስት ባነገበው ሁለንተናዊ ልማት የበኩሉን እንዲወጣ ያነሳሳ ነው ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው፥ በዓሉ ህብረብሔራዊ አንድነት በማጎልበት በህዝቦች መካከል መተማመንን የፈጠረ ኩነት ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ለበዓሉ ስኬት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባኤዎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም