ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል የመላው አፍሪካውያን የነጻነት ዓርማና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል የመላው አፍሪካውያን የነጻነት ዓርማና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሐሳብ አክብረዋል፡፡

የዓድዋ ድል የሉዓላዊነታቸንና የነጻነታችን ምልክት እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያዊውያን የአንድነታችን ማብሰሪያ ውል መሆኑም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያዊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በህብረት የሰሩት ገድል የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ባሻገር የመላው አፍሪካውያን የነጻነት ዓርማ ብሎም የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን የአሸናፊነት ታሪክ በማስቀጠል ለመጪው ዘመን የሚሆን የራሱን ገድል በመስራት ማሸጋገር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡


 

በዚሁ ወቅት የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዳርእስከዳር ታዬ(ዶ/ር)፤ የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት መነሳሳት መሠረት የጣለ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ከፍታ የታየበት እና የቅኝ ገዢዎች ህልም የከሰመበት የጋራ ድል መሆኑን አንስተው ዓድዋ ለዲፕሎማሲው ስኬት መንገድ የጠረገ ድል መሆኑንም አንስተዋል፡፡


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የገጽታ ግንባታ ዳይሬክተር ውብሃ መሃመድ ሁሴን በበኩላቸው ዓድዋ የሀገርን ዳር ድንበርና ክብር የተከበረበት ድል ነው ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞችም በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና የሰንደቅ-ዓላማ ክብር በመስዋዕትነት የተገለጠበት የጋራ ታሪካ መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም