ቀጥታ፡

ተቋማት የሚሰሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ከግምት ያስገባ እንዲሆን በተቀናጀ መልኩ መስራት ይገባል

ሮቤ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- ተቋማት የሚሰሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ከግምት ያስገባ እንዲሆን በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ሃብት ካላቸው ሀገራት ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰው ይህንን ትልቅ ሃብት ለመጠበቅ ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበት አንስተዋል።

በዚህም የብዝሃ ሕይወት ሀብት እንክብካቤ፣ ዘለቄታ ያለው አጠቃቀም የማረጋገጥና ከሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም በፍትሃዊነት ማጋራት የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ማግኘታቸውን ጠቅሰው ተቋማት የሚሰሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ግምት ያስገባ ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

የዱር እንስሳት መኖሪያ የሆነውን ደን በአግባቡ መንከባከብ፣ መጠበቅና ማልማት የሚቻለው ኅብረተሰቡን በማሳተፍ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ናቸው።

በመሆኑም ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ውይይት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው በተለይ በፓርኮችና ቁልፍ የብዝሃ ህይወት አካባቢዎች የሚስተዋሉ ልቅ ግጦሽ፣ የእርሻ መስፋፋት፣ ህገ ወጥ ሰፈራን ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በብዝሃ ህይወት ዘርፍ የሚታዩ ተግዳሮቶችና ስጋቶችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያመላክት ይህ የውይይት መድረክ የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ገመዶ ዳሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማት የሚሰሯቸው ሥራዎች የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን ከግምት ያስገባ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዘለቄታዊ አጠቃቀምን የዕቅዳቸው አካል አድርገው በትኩረት መስራት ከቻሉ የሚፈለገውን ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ብዝሃ ሕይወትን ከመጠበቅ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተምሳሌትነት የሚነሱ መሆናቸውንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም