ቀጥታ፡

ዓድዋ የትኛውንም ፈተናና ችግር በተባበረ ክንድ ማሸነፍ እንደሚቻል ያረጋገጠ የአንድነት ምልክት ነው

ቦንጋ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- ዓድዋ የትኛውንም ፈተናና ችግር በተባበረ ክንድ ማሸነፍ እንደሚቻል ያረጋገጠ የአንድነት ምልክት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ገለጹ።

129ኛው የዓድዋ በዓል በክልሉ ቦንጋ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሮ ውሏል።

አቶ አንድነት በወቅቱ እንዳሉት የዓድዋ ድል ከማሸነፍ ባሻገር አንድነት ኃይል መሆኑን ለዓለም ያረጋገጠ የኢትዮጵያውያን አኩሪ የጋራ ታሪክ ነው።

የዓድዋ ድል ሕዝብና መንግስት፣ ወጣትና አረጋዊ ተናቦ በመዋጋት የተቀዳጁት ድል መሆኑን ጠቅሰው ዛሬም ለፍትሕ እና ለኢኮኖሚ ብልጽግና መረጋገጥ በጋራ መቆምን የሚያስተምር የአንድነት ምልክት ነው ብለዋል።


 

የአሁን ዘመን ትውልድ የዓድዋን ታሪክ ከመዘከር ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቁ ሌሎች ሀገር የሚገነቡ ተግባራት ላይ በመጠንከር የራሱን ዓድዋ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

ከፓናሉ ተሳታፊዎች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ዋና ኢንስፔክተር ብርሃኑ አበራ አባቶቻችን የታጠቀውን የውጭ ወራሪ ተባብረው ድል አድርገው ያስረከቡንን ኢትዮጵያን ዛሬም በአንድነት አጽንቶ የማሻገር ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

ለዚህም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ እና ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመጠቀም በአንድነትና በቁርጠኝነት መሥራትን እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት።


 

ለሀገር አንድነት መጽናት ዓድዋ ትልቅ መሠረት ያለው በመሆኑ ያንን መንፈስ በመጠበቅ ለሀገር ሰላም በጋራ መቆም አለብን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አልማዝ ገበየሁ የተባሉ የበዓሉ ተሳታፊ ናቸው።

አሁን ላይ የዓድዋን መሠረት ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ የተሻለ ከፍታን ለማስረከብ የምንንቀሳቀስበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

አቶ የማነህ ዘውዴ የተባሉ የሀገር ሽማግሌ በበኩላቸው ዓድዋ የሰላምና የአንድነት ምልክት በመሆኑ ትውልዱ ይህን በመረዳት ከመነቋቆር ወጥቶ ሀገሩን መጠበቅ አለበት ብለዋል።

በዓሉ በቦንጋ ከተማ በፓናል ውይይት ሲከበር የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የፀጥታ አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም