የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅርንና አንድነትን የሚያስተምር በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ በልማት ላይ በጋራ ጠንክሮ መስራት አለበት - አባት አርበኞች - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅርንና አንድነትን የሚያስተምር በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ በልማት ላይ በጋራ ጠንክሮ መስራት አለበት - አባት አርበኞች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትንና ስኬትን የሚያስተምር በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ በሀገር ልማት ላይ በጋራ መረባረብ እንደሚገባው አባት አርበኞች ተናገሩ፡፡
ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ቅኝ ያልተገዛች ሀገርን ለአሁኑ ትውልድ ያስረከቡት አብሮነታቸውን በማጠናከርና በጀግንነት ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የአለም ጥቁር ህዝቦች እኩልነትና ነጻነት ትግል መጎልበት ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመጪው እሁድ የሚከበረውን 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ያነጋገራቸው አባት አርበኞች እንዳሉት፤ ድሉ ለወጣቱ የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትንና ስኬትን የሚያስተምር ነው።
በመሆኑ ወጣቱ ጀግኖች አባቶች ያስመዘገቡትን ድል በልማት ለመድገም ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀት፣ ጠንክሮ መስራትንና ሀገርን የማሳደግ አርበኝነት በመፈጸም ሊደግመው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዓሉን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት አባት አርበኛ መኮነን መሸሻ የአሁኑ ትውልድ ለሁሉ ነገር መሰረት የሆነውን እውቀት ለማግኘት ጠንክሮ መማርና ለሀገር እድገት ማዋል አለበት ብለዋል።
ትውልዱ ሀገሩን አልምቶና ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።
አባት አርበኛ 50 አለቃ ዲባባ ጫላ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የመላው የጥቁር ህዝቦች የእኩልነት ትግል አርአያ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረችው በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁንም ሀገር ጸንታና በልጽጋ እንድትቀጥል ትውልዱ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ በልማት ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የሆነውን የዓድዋ ድል በአግባቡ በሚገልጽ መልኩ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመገንባት ወጣቱ ጥበብና ጽናትን በአግባቡ እንዲማርበትና የራሱን ታሪክ ለመስራት እንዲተጋ ማድረጉን የሚገልጸው ደግሞ ወጣት ኖህ ናትናኤል ነው፡፡
ድሉ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ሁኔታዎች ባልተመቻቹበት ሁኔታ የተቀዳጁት ዘመን ተሻጋሪ ድል መሆኑ እኛም ሀገር የወጠነቻቸውን የልማት እቅዶች በማሳካት የራሳችንን ታሪክ መስራት ይኖርብናል ብሏል።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል፡፡