ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሶማሊያ ስምምነቶች ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ትልቅ ፋይዳ አላቸው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ሶማሊያ ያደረጓቸው ስምምነቶች ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ እና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የተሰራው ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ በጉልህ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሊያ ሞቃዲሾ ያደረጉት የሥራ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአዲስ መንገድ መጓዝ መጀመሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ እጣ ፈንታ የተሳሰረ፣ የሶማሊያ ሰላም ለኢትዮጵያም ሰላም መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሁሉ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ተልዕኮ እንደምትሳተፍ የገለጹት አምባሳደር ነብያት፤ እነዚህ የፖለቲካ የሰላምና ደህንነት እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውጤቶች ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ ለቀጣናውና ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በሶማሊያና በቀጣናው ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅሟን መሰረት ያደረገና ነገን አሻግሮ የሚመለከት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሁለቱ ሀገራት ያደረጓቸው ስምምነቶች የሁለትዮሽ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተሳሰረ የልማት ራዕይ እና ቀጣናዊ ምልከታ ያላቸው ጎረቤታሞች መሆናቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጋራ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች በጋራ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁና የአፍሪካን ድምጽ በሚያጎሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በብራዚል በተካሄደው የብሪክስ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያጠናክሩ ውይይቶች ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ያለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት እድል እንደፈጠረ የሚያስገነዝቡ የኢኮኖሚ ትብብር ፎረሞች መከናወኑን አመልክተዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በማይናማር ያሉ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ቶኪዮና ኒውደልሂ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አማካኝነት ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኙ የነበሩ 310 ዜጎች በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም 758 ዜጎች መመለሳቸውን አስታወሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም