ሀገር ዓቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር ዓቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ነገ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡-19ኛው ሀገር ዓቀፍ የፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫል ከነገ ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው 116ኛውን ብሄራዊ የፖሊስ ቀንን በማስመልከት ነው።የውድድሩ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓትም ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኘ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የፖሊስ አባላት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል።
ይህ አኩሪ የፖሊስ የስፖርት ታሪክ እንዲደገምም ፌስቲቫሉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቃል-አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል፥ የፌስቲቫሉ ዓላማ የሠራዊቱን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር፤ ፖሊሳዊ ቁመናን በማሳደግ የተልዕኮ አፈፃፀምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲሁም በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ ሀገርን ወክለው የሚሳተፉ የፖሊስ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሆነ ገልጸዋል።
ውድድሩ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደር እና በክልል የፖሊስ ተቋማት መካከል እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በሚካሄደው በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንደ ሀገር ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው መነጋራቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።