የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለሱዳን ስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለሱዳን ስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ አደረጉ
አሶሳ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጠልለው የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችን በመጎብኘት ሰብዓዊ ድጋፍ አድርገዋል።
በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ታላቁ የረመዳን ወር ደግሞ የደግነት፣ የርህራሄ፣ የመስጠት፣ የተቸገሩትን የማገዝና የመደገፍ እሴቶችን የሰነቀ ነው።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጠልለው የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችን በመጎብኘት ድጋፍ አድርገዋል።
ከድጋፉ በተጓዳኝ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም ለስደተኞች እየተደረገው ስላለው ድጋፍ የክልሉን መንግስት አመስግነዋል።
የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ የሰብዓዊነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስደተኞቹን በቋሚነት ለመደገፍ ሁሉም የበጎ አድራጎት አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን በበኩላቸው የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሰላም እና በልማት ስራዎች ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብዝሃነትን በማቀፍ በእኩልነትና ፍትሃዊነት በማስተናገድ ላይ መሆኑን አንስተው ለተፈናቃዮችም ተገቢው እገዛና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።