ረመዳን ወርን በመደጋገፍና በመረዳዳት ማሳለፍ ይገባል- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ረመዳን ወርን በመደጋገፍና በመረዳዳት ማሳለፍ ይገባል- ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፦ ህዝበ ሙስሊሙ በታላቁ ረመዳን ወር የመረዳዳትና አብሮነት እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ ማሳለፍ እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን በሰጡት መግለጫ ወሩ ሠናይ ምግባራት የሚጠናከሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ህዝበ ሙስሊሙ የመተባበርና የመረዳዳት እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ ወሩን ማሳለፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ከምግብና መጠጥ ከመታቀብ በላይ ይቅር መባባል እና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀው፤ በረመዳን ወር ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ የተለያዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሼህ ሁሴን በሽር በበኩላቸው በረመዳን ፈጣሪን ምህረትን መለመን ዋነኛ ስራ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በጾሙ ወቅት የሚሰሩ መልካም ስራዎች ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሚልቁ መሆናቸውን ገልጸው ሁሉም ለመልካም ስራ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።