ቀጥታ፡

ከአድዋ የተረከብነውን የጀግንነት ድል በማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያላትን አገር እንገነባለን

ሰመራ/ቦንጋ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፦ ከአድዋ የተረከብነውን የጀግንነት ድል በማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያላትን አገር እንገነባለን ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ዱላ ገለጹ።

129ኛውን የአድዋ ድል በዓል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

በሰመራ ከተማ በበዓል አከባበሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑመር ዱላ " ከአድዋ የተረከብነውን የጀግንነት ድል በማስቀጠል ጠንካራ አንድነት ያላትን አገር እንገነባለን" ብለዋል።

አድዋ ከሁሉም የኢትዮጵያ ጫፎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ለአገር ክብርና አንድነት የተዋደቁበትና ድል ያደረጉበት አኩሪ የድል ታሪካችን ነው ብለዋል።

በጥቁር ህዝቦች ላይ የተጣለው የመከራ ቀንበር እንዲወድቅ አድዋ የድል አቅጣጫን ያመላከተ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን የመላው አፍሪካ ኩራት የሆነውን የድል ቀን የዛሬው ትውልድ በጀግንነት ማስቀጠል ይኖርበታል ሲሉም አቶ ዑመር አሳስበዋል።

በተመሳሳይም በዓሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች የአንድነትና የኩራት ምልክት ነው።

አባቶቻችን ሀገርን ለማጽናት የከፈሉት ዋጋ የዘረኝነትና ጥቁሮችን የበታች አድርጎ የመመልከት እሳቤን በመታገል አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በቦንጋ ከተማ እየተከበረ ባለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፓናል ውይይት ላይ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም