በ259 የምግብ አምራች፣ አስመጪዎችና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል- ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በ259 የምግብ አምራች፣ አስመጪዎችና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል- ባለሥልጣኑ
አዳማ፤ የካቲት 21/2017 (ኢዜአ)፦ በግማሽ ዓመቱ የምርት ጥራት ጉድለት በተገኘባቸው 259 የምግብ አምራቾች፣ አስመጪዎችና ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለፀ።
በባለስልጣኑ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፋይዛ ቢያ እንዳሉት በመላ ሀገሪቱ ቁጥጥር ከተደረገባቸው የምግብና መጠጥ ድርጀቶችና ኢንዱስትሪ ተቋማት መካከል የጥራት ጉድለት በተገኘባቸው 259 የምግብ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
ከነዚህም መካከል በ98 ድርጅቶች እገዳ፣ በ31 ድርጅቶች የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በቀሪዎቹ ደግሞ ስረዛ እና እሸጋ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በስድስት ወራት ውስጥ በድርጅቶቹ ለጤና አደገኛ የሆኑ ምግቦችንና መድሀኒቶችን ማስወገድ መቻሉን ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት የተለያየ ችግር የተገኘባቸው የትምባሆ ምርቶች እንዲወገዱ መደረጉን አስታውቋል።
በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ከ209 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብ እና የመድኃኒት ምርቶች ማስወገዱም ተገልጿል።