ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ዳግም እየተጠናከረ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዳግም እየተጠናከረ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ አገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ ከፖለቲካ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መካከል ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያለ ግንኙነት በአዲስ መንፈስ ለማጠናከር የተከናወነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሊያ ሞቃዲሾ ጉብኝት ማድረጋቸው የግንኙነቱ መሻሻል እና በአዲስ መንገድ መጓዝ መጀመሩ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

ጉብኝቱን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ግንኙነት በአዲስ መንገድ መጓዝ መጀመሩ በሁለትየሽ ግንኙነት ላይ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት ሁሉን አቀፍ ልማት እጣ ፋንታቸው የተሳሰረ እና የሶማሊያ መረጋጋት የኢትዮጵያ መረጋጋት መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶች ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን የገለጹት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሠላም ማስከበር እና ማረጋጋት ተልዕኮ እንደምትሳተፍም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ አገራት በደረሱባቸው ስምምነቶች መሰረት ሽብርተኝነትን በጋራ በመፋለም በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኀንነት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚያስችላቸውም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተከተለችው ጥበብ የተሞላበት የዲፕሎማሲ መንገድ ለውጤት አብቅቷታል ነው ያሉት።

አምባሳደር ነብያት ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንጻር የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት እና የኢትዮጵያ የንግድ እና ኢኮኖሚ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄዱ አስታውሰዋል።

በፎረሙ ላይ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረቻ ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ መሳሪያዎች ማምረቻ፣ በመሠረተ ልማት እና በኢንፎርሜሽ እና ኮሙኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ(አይ ሲቲ) ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በማይናማር በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከማይናማር ወደ ታይላንድ የተሻገሩ 246 የሚጠጉ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ አስፈላጊውን የሰነድ ማጣራት እና የጉዞ ዝግጅት ድጋፍ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ሕብረተሰቡ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ውል ወዳልተፈጸመባቸው አገራት በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አሳሳች ማስታወቂያዎች በመታለል ለአደጋ እንዳይዳረግ ጥንቃቄ ማድረግ ማሳሰባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም