ቀጥታ፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የብሔራዊነት ትርክትን እያጠናከረ ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አርባምንጭ፤ የካቲት 21/2017 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ የብሔር፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መከበር የብሔራዊነት ትርክት እንዲጠናከር በተግባር እያረጋገጠ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

በ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበር አስተዋጾ ላደረጉ አካላት እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የብሔር፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የብሔራዊነት ትርክት እንዲጠናከር በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ጉልህ ፋይዳ ማበርከቱን ገልጸዋል።

''ሀገር የትርክት ውጤት ናት'' ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ ባለፉት ጊዜያት በጥሩም ሆነ በመጥፎ የፈጠርናቸው ትርክቶች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የየራሳቸው ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል።

የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የተሳካ እንዲሆን የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ድርሻቸው ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

"ብሔራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሕዳር 29/2017 ዓ/ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም