ሠራዊቱን ለተሠጠው ተልዕኮ የማዘጋጀት ስትራቴጂያችን ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱን ለተሠጠው ተልዕኮ የማዘጋጀት ስትራቴጂያችን ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ሠራዊቱን ለተሠጠው ተልዕኮ የማዘጋጀት ስትራቴጂያችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ሌትናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ይህን የተናገሩት በአየር ኃይሉ አካዳሚ አመራር ኮሌጅ ሲሰለጥኑ ለቆዩ ከፍተኛ መኮንኖች ነው።
አመራሩ በተሰጠው የአመራርነት ስልጠና በስሩ የሚመራውን ሠራዊት በሁለንተናዊ መልኩ በግዳጅ አለኝ አስተሳሰብ መቃኘት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አመራሩ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ከባቢያዊ እና ውስጣዊ ሁኔታን ከምን ጊዜውም በላቀ ሁኔታ መረዳት ይኖርበታል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት ዓመታት በትጥቅ አቅም ግንባታ፣ በውጊያ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሰው ኃይል ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ያከናወናቸው ሰፋፊ ስኬታማ ስራዎች ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱ ከሠልጣኝ መኮንኖች ጋር ችግኝ የመትከል መርሐ-ግብር መከናወኑን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።