የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍን ተሳትፎ ይጠይቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍን ተሳትፎ ይጠይቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ በገጠራማው የሀገሪቷ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ብርቱ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሶላር ኢነርጂ ልማት ማሕበር የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ ዛሬ በሳይንስ ሙዚዬም ተከፍቷል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከዋናው መስመር የራቁና አብላጫው ሕዝብ በሚኖርባቸው የሀገሪቷ ገጠራማ አካባቢዎች አማራጭ የሀይል ምንጮችን በመጠቀም የሃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል።
በተለይም በገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ትግበራ በሀገሪቷ ገጠራማ አካባቢዎች ከፀሐይ ኃይል የመነጨ ሃይል ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል በገጠራማው ክፍል በተቋማትና ግለሰቦች ቤት የሶላር ኢነርጂ አማራጭ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አውስተዋል።
የሀገሪቷን የሀይል ተደራሽነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ግን የግል ዘርፍ ብርቱ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ነው ያነሱት።
በዕለቱ የተከፈተው ዐውደ ርዕይም በዘርፉ የተሰማሩ የግሉ ዘርፍ ተዋኒያን ትስስርና ቅንጅት ለማጎልበት እንደሚያግዝ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሶላር ኢነርጂ ልማት ማሕበር ዋና ዳይሬክተር የምስራች ሲሳይ ፣በገጠራማ አካባቢ ከሶላር የሚመነጭ ኃይልን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ማሕበሩ የራሱን ተሳትፎ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዕለቱ የተከፈተው ዐውደ ርዕይ የዘርፉ ቴክናሎጂዎችን ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።