የኢትዮ-ኢንዶኔዥያ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሯል- አምባሳደር አልቡሲራ ባስኑር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኢንዶኔዥያ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሯል- አምባሳደር አልቡሲራ ባስኑር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የሚያጠናክሩ ስራዎች ባለፉት ዓመታት በስፋት መከናወናቸውን በኢትዮጵያ ተሰናባቹ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሲራ ባስኑር ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል።
ትብብራቸውን ለማጠናከርም ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
ለአብነትም በትምህርት መስክ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጋራ መስራት የሚያስችሏቸውን በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በስራ ቆይታቸው የኢትዮጵያንና የኢንዶኔዥያን ትብብር ወደላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ በርካታ አጀንዳዎችን በመለየት ወደ ተግባር ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
ከአምስት በላይ የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች በመድሃኒት፣ በምግብ እና መጠጥ ማምረቻ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በጥቅሉ ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ትብብር እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህ በውጤታማነት እንዲቀጥል ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
አምባሳደር አልቡሲራ ባስኑር በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ቆይታ አጠናቅቀው በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ትናንት ስንብት እንደተደረገላቸው ይታወቃል።