አብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
አብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት የበልግ ወቅት በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው፡፡
ለአካባቢዎቹ የበልግ ወቅት እስከ 55 በመቶ የሚሆን ድርሻን የሚይዝ ዋነኛ የዝናብ ወቅት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮ የበልግ ወቅት አብዛኛው የበልግ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸውም የአየር ትንበያዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የደመና ሽፋን መጨመሩን ተክትሎ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መደበኛ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ በአንዳንድ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ዝናብ መጀመሩን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ በቀጣይም የደመና ሽፋን መጨመሩን ተከትሎ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሚጥለው የዝናብ መጠን ለግብርና ስራም ይሁን ለሌሎች ተያያዥ ስራዎች ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሚሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የዝናብ መጠኑ አነስተኛ ሊሆን ስለሚችል ከሚጥለው የዝናብ መጠን ውሃን በአግባቡ የማጠራቀም ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በአገሪቱ ካሉ ሶስት ወቅቶች መካከል አንዱ የሆነው የበልግ ወቅት ከየካቲት እስከ ግንቦት መጨረሻ ያለውን ወቅት የሚያካትት ነው፡፡