ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር አበክረው እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሊያ መንግስት የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ በሶማሊያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ሞቃዲሾ ሲደርሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ መሐሙድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለፉት ጥቂት ወራት የነበራቸውን ገንቢ ውይይቶች ተከትሎ የመጣ እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት የመመለስን ስራ የሚያጠናክር መሆኑን የሀገራቱ መንግስታት የጋራ አቋም መግለጫ አመልክቷል።
የሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገራቱ ህዝቦች ጥልቅ የሆነ ታሪካዊ ግንኙነት እና የሚያስተሳስራቸው የጋራ ድንበር እንዳላቸው ያወሳው መግለጫው፥ በዚህ ረገድም በዲፕሎማሲያዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብር መተማመንን መገንባት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ብልጽግናን እውን የማድረግ የጋራ ራዕይ ያላቸው ሀገራት ናቸው ብሏል።
በዚህ ረገድም የሀገራቱ መሪዎች ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጡ፣ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያሳልጡ እና የህዝብ-ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ ስትራቴጂካዊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው መግለጫው ያመለከተው።
በተጨማሪም መሪዎቹ በአንካራ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የቴክኒክ ውይይት መጀመሩ መልካም የሚባል መሆኑን እና ይህም ሀገራቱ ገንቢ ውይይት እና ትብብር ለመፍጠር ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።
መሪዎቹ በሶማሊያ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል እና በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች መካከል የደህንነት ትብብር ለማጠናከር እና ቀጣናዊ መረጋገትን ለማስፈን ለደረሱበት የጋራ መግባባት እውቅና ሰጥተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸውን በማራመድ፣ሰላም እና ደህንነትን በማረጋገጥ እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ዜጎቻቸውን አልፈውም የአፍሪካ ቀንድን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን መግለጫው አትቷል።