በዶክተር አንዱዓለም ዳኜ ግድያ ላይ በዋና ተሳታፊነት የተጠረጠረ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በዶክተር አንዱዓለም ዳኜ ግድያ ላይ በዋና ተሳታፊነት የተጠረጠረ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ

ባህር ዳር፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በዶክተር አንዱዓለም ዳኜ ግድያ ላይ በዋና ተሳታፊነት የተጠረጠረ ግለሰብን በቁጥጥር ስር በማዋል ተባባሪዎችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
ዶክተር አንዱዓለም ዳኜ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትና የጉበት፣የቆሽትና የሃሞት መስመር ሳብ ስፔሻሊቲ ሃኪም፣ መምህር፣ተመራማሪና በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር እንደነበሩ ይታወሳል።
የመምሪያው ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ዶክተር አንዱዓለም ዳኜ በተለምዶ ቆሸ በሚባለው ቦታ ጥር 24/2017 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ላይ መገደላቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስም ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ፣በማን እንደተፈጸመና ፈጻሚዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።
በተደረገው ጥብቅ ክትትልም በዋና ገዳይነት የተጠረጠረው እሱባለው ነበረ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርምራ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፥ ተባባሪዎቹን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀርቦ የግድያ ወንጀል መፈጸሙን ያመነ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሌሎች ወንጀሎች የተሳታፈ እንደነበረ የኋላ ታሪኩ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ከክልሉ ፍትህ ቢሮ፣ ከፖሊስ ኮሚሽን፣ ከባህርዳር አስተዳደር ፖሊስ መምሪያና ከሰሜን ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የተውጣጣ የመርማሪ ቡድን ተዋቅሮ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።