ቀጥታ፡

የጊኒ ወርም በሽታን ለማጥፋት በተከናወኑት ተግባራት ስርጭቱን መቀነስ ተችላል - ጤና ሚኒስቴር

ጋምቤላ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት ዓመታት የጊኒ ወርም በሽታን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በተከናወኑ ተግባራት ስርጭቱን መቀነስ መቻሉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስታወቀ።

የጊኒ ወርም በሽታን ለማጥፋት በፈረንጆች በ2024 የተከናወኑ ስራዎችን የሚገመግም 29ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ መድረክ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሽታውን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በተከናወኑት ስራዎች ስርጭቱ በእጅጉ ቀንሷል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው በላፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በበሽታው የተጠቃ ሰው ያለመኖሩን ጠቅሰው፤ በእንስሳት ላይም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በአንድ ውሻና ሁለት ዝንጀሮዎች ላይ ብቻ መገኘቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተደረገው ጥረት የስርጭት መጠኑን መቀነስ ተችሏል።

በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የጥናት፣ የምርምርና የቅኝት ስራዎችን በማጠናከር በሽታውን ለማጥፋት በቅንጅትና በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

መድረኩ በሽታውን ለማጥፋት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ውጤታማ ስራዎችን ለመከወን የሚረዳ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) እንዳሉት ባለፉት 30 ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች የበሽታውን ስርጭት መጠን መግታት ቢቻልም ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አልተቻለም።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በክልሉ በቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ያለመሆን ችግር መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዓመታዊ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም