የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፡- የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ወደ ውድድር ይመለሳል።
ውድድሩ የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ ከየካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እረፍት ላይ ነበር።
የ20ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
ሃዋሳ ከተማ በ15 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሲገኝ ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ በ30 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ከምሽቱ 12 ሰዓት መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቀሌ 70 እንደርታ በተመሳሳይ 22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
መርሐ ግብሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ሲዳማ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሑል ሽሬ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።
የ20ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
ሊጉን ኢትዮጵያ መድን በ35 ነጥብ ሲመራ ሀዲያ ሆሳዕና በ30፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 እና መቻል በ27 ነጥብ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ፣ ሃዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ጠና ውስጥ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ በስምንት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።
የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ሰባት ግቦች ይከተላሉ።