ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ለመጀመር እየተሰራ ነው - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ መኪዮ መሐመድ ገለጹ፡፡


 

ሚኒስትር ዴዔታውን ጨምሮ የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን፣ የስፖርት ዘርፍ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ ፎረንሲክ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ መኪዮ መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የጉብኝቱ አላማ የኢትዮጵያ ፎረንሲክ ኢንስቲትዩት ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ላቦራቶሪ ግንባታ ምቹ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡


 

ኢንስቲትዩቱ የወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮችን ለመመርመር ያደራጃቸው ላቦራቶሪዎችና የዘረጋቸው የአሰራር ስርዓቶች የሚደነቁና ሀገርን የሚያኮሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በጉብኝቱም ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት በተጨማሪ ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ምቹ ቦታ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአለም የምትታወቅበትን የስፖርት ዘርፍ ውጤታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ፎረንሲክ ኢንስቲትዩት የፎረንሲክ ምርመራ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ በበኩላቸው፤ ፀረ አበረታች ቅመሞችን መጠቀም የወንጀል ፍሬ ተብለው ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ ማዕከል ማቋቋም የሚችል አቅም እየገነባ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ለመነሻ የሚሆኑ መሳሪያዎች እንዳሉት አረጋግጠዋል።

ምርመራውን አሁን ካለው የሰው ሃይል እና የቴክኖሎጂ አቅም በተወሰነ ደረጃ መጨመር ከተቻለ ምርመራውን በአጭር ጊዜ መጀመር እንደሚቻልም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል በኢንስቲትዩቱ ያሉ የመመርመሪያ ላቦራቶሪዎች ለፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ መነሻ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የምርመራ ማዕከሉን በአጠረ ጊዜ ለማቋቋም አለም አቀፍ መስፈርቶችን የማሟላት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ በተለይ የፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ ለማድረግ አዳጋች እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሀገር ውስጥ ለመጀመር የተያዘው ውጥን የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም