ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየር ሰላም መሰረታዊ ነገር ነው - ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየር ሰላም መሰረታዊ ነገር ነው - ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፡- አንድ ሀገር ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየር ሰላም መሰረታዊ ነገር መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ገልጿል።
ፓርቲው ሰላምን አብዝተን እንሻለን! በሚል ሀሳብ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት አንድ ሀገር ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየር ሰላም መሰረታዊ ነገር ነው ብሏል።
በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት፤ ሰርቶ መብላት፤ ወልዶ መሳም አይቻልም ሲልም ገልጿል፡፡
ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንሰሳት፤ ለዕፅዋት፤ ለጋራ ሸንተረሩ፤ ለወንዞችና ጅረቶችም እጅጉን አስፈላጊ ነው በሏል ፓርቲው በመልዕክቱ።
በአንፃሩ ደግሞ ጦርነት አውዳሚ፣ ገዳይ፣ ሀገር አፍራሽ፣ ዜጎችን ሀገር አልባ የሚያደርግ፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን የሚያስፋፋ፣ የጦርነት ጥሩ፤ የሰላም መጥፎ የለም፤ ለዚህም ነው ሰላምን አብዝተን የምንሻው በማለትም ገልጿል።
የዜጎቻችን መሰረታዊ ፍላጎት ሰላም፤ ልማት፤ ነፃነትና ዴሞክራሲ ነ ው ያለው ፓርቲው፤ ለዚህም የብልጽግና ፓርቲ ሰላም፤ ሰላም፤ ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለዜጎቿ፤ ሰላም ለአፍሪካ፤ ሰላም ለአለም እያለ በየመድረኩ አብዝቶ የሚሰብከው ብሏል።
ለዚህ ነው ሰላማዊ ትግልን አሻፈረኝ በማለት ነፍጥ አንስተው የሸፈቱ ሃይሎችን እንኳ ሳይቀር ዛሬም ድረስ እጃችንን ዘርግተን ደጋግመን የሰላም ጥሪ የምናስተላልፈው ሲልም አስታውቋል።
እንደ ፓርቲ የሰላም አማራጭ የምናስቀድመው ህዝባችን የባሩድ ሽታ ሳይሆን የሰላም አየር መተንፈስ አለበት፤ ለህዝባችን ልማት ይገባዋል፤ ህዝባችን የለውጡ ትሩፋት ተቋዳሽ መሆን እንዳለበት ስለምናምን ነውም ነው ያለው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት በብዙ ተግባሮች የሚገለፅ ነው ያለው ፓርቲው፤ በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ተቋማት፤ መሰረተ ልማቶች እና ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በበጀትም ሆነ በሌሎች ቁሳቁሶች መላው ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የተሄደው ርቀት ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት ለአለም ያሳየ ነውም ብሏል።
ፓርቲያችን በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው የተጀመረው አካታች ሀገራዊ ምክክር በስኬት ተጠናቆ የኢትዮጵያን የዘመናት የፖለቲካ ስንክሳር እንዲዘጋ፤ በልዩነትና በግጭቶች አያያዛችን ላይ ዘላቂ የመፍትሔ መንገዶች እንዲቀይስ፤ ለተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፕሮግራም ተግባራዊነትና ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት፤ አዎንታዊ ዘላቂ ሰላማችንን እያስተጓጐሉ ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቅጣጫ ማስቀመጡ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነዉ።
ኢትዮጵያ በብዙ ፀጋዎች የተሞሸረች እንዲሁም እድሜ ጠገብ ሀገር ሆና ሳለ በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች ሰላሟን አጥታ ፀጋዎቿን ተጠቅማ ወደ ብልጽግና ማማ መውጣት አልቻለችም ሲልም ገልጿል።
እነዚህ ምክንያቶች ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን እየፈተኑ ቢገኙም ትናንት አባቶቻችን በቋንቋ፤ በባህል፤ በሃይማኖት፤ በብሔር ሳይለያዩ አንድ ሆነው ወራሪውን ፋሺስት ጣሊያን እና የውስጥ ባንዳን ተዋግተው ማሸነፋቸውን ጠቅሶ የጥቁሮች ሁሉ ድል የሆነውን የአድዋ ድልን በማስመዝገብ አለምን ጉድ እንዳሰኙ ሁሉ እኛም የአባቶቻችን ልጆች ስለሆንን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክርን ኢትዮጵያና ህዝቦቿን የሚገጥሙ ፈተናዎችን ሁሉ በድል ተሻግረን ወደ ብልፅግና ሰገነት መውጣታችን አይቀሬ ነው ሲልም ገልጿል።
ሰላምን ሁላችንም አብዝተን እንፈልጋለን ለብልጽግና መሰረት የሆነውን የሰላም እሴት መጠበቅ ለዘላቂ ሰላም በጋራ መቆም ደግሞ የጋራ ሃላፊነት ነው ብሏል ፓርቲው በመልዕክቱ፡፡