ኒጀር በውትድርና እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነች - ኢዜአ አማርኛ
ኒጀር በውትድርና እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነች
አዲስ አበባ፤የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ኒጀር በውትድርና እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምትፈልግ እና በጋራ ለመስራትም ቁርጠኛ መሆኗን ሌተናል ጄኔራል ሳሊፎ ሞዲ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በኒጀር ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሌተናል ጀኔራል ሳሊፎ ሞዲ የተመራውን ወታደራዊ ልዑክ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይም በርካታ ወታደራዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት፥ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን ችግር የሚፈታው በራሳቸው በአፍሪካዊያን ነው የሚል የፀና አቋም እንዳላት ገልፀዋል፡፡
በመተማማን እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እና የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ግንኙነት እስካለ ድረስ አፍሪካ ለሌላው ዓለም አርአያ የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለምም ብለዋል።
የኒጀር ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ሌተናል ጀኔራል ሳሊፎ ሞዲ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ሀገራችንም ሆነች አህጉራችን አፍሪካ ችግር በገጠማት ጊዜ ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ ኢትዮጵያ ዋጋ ከፍላለች ብለዋል፡፡
በውይይቱ ወቅትም፥ በውትድርና እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እና በጋራ ለመስራትም ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰራዊት ልምድ እና የወታደራዊ ትምህርት ቤቶችን ተሞክሮ በመቅሰም ኒጀርን ታላቅ የሚያስብል ዘመናዊ የውትድርና ተቋም መገንባት እንደሚችሉ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አትዮጵያ አሸባሪ ቡድኖችን የመደምሰስ ልምድ ያላት ቢሆንም ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ አሸባሪ ቡድኖቹ ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ስለሚዘዋወሩ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለአንድ ዓላማ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል፡፡
ሠራዊቱ ከህዝብ ጋር ያለው ቁርኝት ምን እንደሚመስል ሀሳብ ያነሱት የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከራስ በፊት ለህዝብ የሚለውን እሴቱን በተግባር የሚፈፅም፤ ለሀገሩ ክብር እና ሰንደቁ ክብር የማይተካ ውድ ህይወቱን በፍቅር የሚለግስ ጀግና ሰራዊት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣዮቹ ቀናትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በተቋማዊ ሪፎርሙ ያመጣቸው ለውጦች ምን እንደሚመስሉ ተሞክሮ ለመውሰድ በልዩ ልዩ የተቋሙ ክፍሎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ መገለጹን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።