የኢትዮጵያ የስደተኞች አያያዝ ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ነው_ የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የስደተኞች አያያዝ ለሌሎች አገራት አርዓያ የሚሆን ነው_ የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን
አሶሳ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች አያያዝ ለሌሎች አገራትም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው መብጎሪ ገለጹ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዑራ ወረዳ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞችን አያያዝ በተመለከተ በአሶሳ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻዲሊ ሐሰን፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው መብጎሪ፣ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሰደር ሶፊ ኤፍ.ኤምስበረገር፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው መብጎሪ፤ በኢትዮጵያ የሱዳን ተፈናቃዮች አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የስደተኞቹ አያያዝ ለሌሎች አገራትም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለመንግስት ጥረት መሳካት የሁላችንም እገዛ ያስፈልገዋል ብለዋል።
በመሆኑም በስደተኞች መጠለያና አካባቢው የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በማስፋፋት ለስደተኞች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም በትኩረት እንሰራልን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስደተኞች አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አንስተው የሁሉም አጋር አካላት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ በሱዳን የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች በስደት ላይ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ የሱዳን ዜጎችን ተቀብሎ በማስተናገድ አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰው የስደተኞቹ አኗኗር ከህብረተሰቡ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራቸው መደረጉንም በአድናቆት አንስተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን፤ በክልሉ አሁን ላይ የሱዳንን ጨምሮ ከ108 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ተጠልለው የሚገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ስደተኞች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ ተቋማት የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ እና ድጋፍም እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተው ከብዛታቸው አንፃርና ከሚፈለገው ድጋፍ አንፃር የለጋሽ አገራት እገዛ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዑራ ወረዳ ከ13 ሺህ በላይ የሱዳን ስደተኞች የሚገኙ መሆኑም ታውቋል።