ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት አትላስ ሊዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የኢትኖግራፊና የቋንቋ ባህሪያትን ያካተተ የማንነት አትላስ ማዘጋጀት የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የማንነት አትላሱን ለማዘጋጀት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ፈርመውታል።

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነትና የአንድነት እሴት በምርምር ማጎልበትና ማጉላት ይጠይቃል።

ቀደም ብሎ የነበረውን የኢትኖግራፊና የቋንቋ ባህርያት ያቀፈ አትላስ ዝግጅት ጥያቄ መሰረት በማድረግ ሶስቱ ተቋማት ስምምነት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት በቀጣይም ዝርዝር ዕቅድ ወጥቶ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የማንነቶች አትላስ ለዘርፉ አጥኚዎች ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቋንቋዎችን ባህሎችንና ልምዶችን የማጥናት የመሰነድ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

የአትላስ ዝግጅት ጥናቱን ትኩረት በመስጠት ወደ ተግባር እንደሚያስገባና ለውጤታማነቱ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ለረጅም ዓመታት በባህልና በቋንቋ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።

ይህንን ልምዱን በመጠቀም አትላሱን የማዘጋጀት ሚናውን በአግባቡ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም