አጽዋማትን በአብሮነትና በመረዳዳት ማሳለፍ ይገባል- የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
አጽዋማትን በአብሮነትና በመረዳዳት ማሳለፍ ይገባል- የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦ አጽዋማትን በመደጋገፍ እና የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ማሳለፍ እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዐቢይ ጾም ያለፈው ሰኞ ይዘዋል፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ፆምን ደግሞ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይይዛሉ፡፡
አጽዋማቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና በእስልምና እምነት ዘንድ ትልቅ ቦታ ያላቸው በምግባርና በጽሞና የሚከወኑ ናቸው፡፡
በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የጥናትና ምርምር መምሪያ ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል መረዳዳትና መተጋገዝ የአብሮነት እሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የጾም ወቅቶችን መረዳዳትና አብሮነትን በሚያጎሉ ተግባራት እንደሚያሳልፉ ገልጸው፤ ይሄ መልካም እሴት በዐቢይ ጾም ወቅትም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባኤ ምክር ቤት የኡለማ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሼህ መሀመድ ዘይን ዘህረዲን ኸሊል በበኩላቸው፤ የረመዳን ጾም ህዝበ ሙስሊሙ ለተቸገሩ በመርዳት እና በመተጋገዝ ከፈጣሪው ይበልጥ የሚቀርብበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና እስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለዓለም አርዓያ የሚሆን ዘመን የተሻገረ መተሳሰብና መደጋገፍ እንዳለ ያነሱት አባቶቹ በሁለቱ ታላላቅ አጽዋማት ወቅትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
አጽዋማቱ በተመሳሳይ ወቅት መጀመራቸው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የመተባበር እና የመተሳሰብ አስተምህሮውን የበለጠ ገቢራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡