ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር ያካሂዳል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።
ቡድኖቹ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ካምፓላ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ዩጋንዳ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረውልድ የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ ማግስት ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ማድረጉን ኢዜአ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ተጋጣሚውን ከሁለት ግብ በላይ ልዩነት ማሸነፍ ይኖርበታል።
ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ዩጋንዳን ካሸነፉ በሁለተኛው ዙር ከታንዛንያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
ከዛሬው ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ብርቱካን ገብረ ክርስቶስ እና ረሒማ ዘርጋው በክብር እንደሚሸኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ 12 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።