የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ድል አድራጊነት በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ የታየበት ገድል ነው - የታሪክ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2017(ኢዜአ)፦የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ድል አድራጊነት በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ የታየበት የጥቁር ህዝቦች ገድል መሆኑን የታሪክ ምሁራን ገለጹ፡፡

ዓድዋ ላይ ጀግንነትን፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና የአልገዛም ባይነት ወኔን ከጦርና ጎራዴ ጋር የታጠቁ ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታገዘውን የጣሊያን ወራሪ ጦር ድል በማድረግ የሀገራቸውን ክብርና ሉዓላዊነት አጽንተዋል፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የባርነትን ቀንበር አሽቀንጥረው በመጣል እኩልነታቸውን እና ነፃነታቸውን የተጎናጸፉበት የታሪክ አምድ ነው፡፡

የሀገር ፍቅር፣ የጋራ ዓላማ፣ የመንፈስ ጥንካሬ፣ ጽናት፣ የአልሸነፍ ባይነት ወኔ፣ ትብብር እና የድል አድራጊነት ጀብዱ የዓድዋ ድል ትሩፋቶች ናቸው፡፡

የታሪክ ተመራማሪውን ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዓድዋ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ጥቁር ህዝቦች ኩራት ነው፡፡

ጥቁር ህዝቦች ከጭቆና ቀንበር የወጡበት ነጻነታቸውን ያወጁበት፤ ቅኝ ገዥዎች ደግሞ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የወደቁበትና አንገት የደፉበት ድል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዓድዋ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ሀገራቸውን በአንድነት፣ በፅናት፣ በመስዋዕትነት ከነክብሯ ያቆዩበት ዘመን አይሽሬ ገድል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከፍ ያለ ቦታ እንዲኖራት ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ የዚህ ዘመን ትውልድ የአንድነት ምልክትነቱን ገዥ ትርክት ለማስረጽ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡


 

የዓለም ጥቁር ህዝቦች ማዕከል ዋና ጸሀፊ ጸጋዬ ጨማ  ዓድዋ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ድል ብቻ ሳይሆን የመፃኢ ጊዜም ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ቅኝ ገዥዎችን ድል ያደረጉበት አንገታቸውን ቀና ማድረግ የቻሉበትን ድል ያጎናጸፈ መሆኑንም ተናገረዋል፡፡

ዓድዋ በሰው ልጆች ታሪክ የጥቁር ህዝቦች ያደርጉታል ተብሎ የማይታመን ተጋድሎ የተፈጸመበትና የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት አየር መንፈስ የጀመረበት አኩሪ ድል ነው ብለዋል፡፡ 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ግሩም ግርማ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በዓለም አደባባይ የገለጸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል በመሆኑ ገዥና አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት ሌላኛውን ዓድዋ መድገም ይገባል ብለዋል፡፡

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከበራል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም