የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተዋንያን በሕግ ተጠያቂ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተዋንያን በሕግ ተጠያቂ እየተደረጉ ነው
አዳማ፤ የካቲት 18/2017( ኢዜአ)፦ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተሳታፊዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሕግ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ገለጹ።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ለኢዜአ እንዳሉት በርካታ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እየዳረገ ያለው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለቱ የበዛና በርካቶች የሚሳተፉት በመሆኑ ወንጀሉን ለመከላከል የጋራ ጥረት ይጠይቃል።
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል፣ ባንኮክ፣ ማይናማር እና ቬትናም ድንበር ድረስ የተዘረጋ ሰፊ መረብ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ሰዎች ከሕገ ወጥ ፍልሰት ይልቅ በሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ እስከ የመን፣ ሊቢያና አውሮፓ በሰው አካል የመነገድ፣ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር የማስወጣትና የማስኮብለል ወንጀል ተዋኒያን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ከአገራትና ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር የወንጀል ተሳታፊዎችን በመያዝ በሕግ ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በጉዳዩ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን 88 መዝገቦች በማደራጀት ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተለይም በበይነ መረብ የማጭበርበር ወንጀል ቁልፍ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አንስተዋል።
በኤጀንሲ ሽፋን በሕገ ወጥ መልኩ የተደራጁ ደላሎችና አገናኞችን ጨምሮ የወንጀሉ ተዋናዮችን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።