የሴቶች የንግዱ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት መንግስት ትኩረት ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች የንግዱ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት መንግስት ትኩረት ሰጥቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ ሴቶች በንግዱ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ምስረታና ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) በምስረታ ጉባዔው ላይ እንዳሉት የተመሰረተው ማህበር በሴት ነጋዴዎች ላይ የሚያጋጥሙ ስርዓታዊና መዋቅራዊ እንቅፋቶችን በማቃለል የሴት ነጋዴዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል።
አደረጃጀቱ የንግድ ስርዓትን አካታችነት፣ ጤናማነትና ተደራሽነት የሚያሰፋና ስራ ፈጠራን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ሴቶች በንግዱ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሚኒስቴሩ የላይሰንሲንግ እና ሬጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈጻሚ መስከረም ባሕሩ ማህበሩ አካታች መልክ ያለው እና ብርቱ ስራ ፈጣሪ ሴቶችን ያቀፈ ነው ብለዋል።
ቀደም ብሎ የነበረው የሴት ነጋዴዎች አደረጃጀት ከህጋዊነት አኳያ ብዙ ክፍተቶች ስለነበሩበት በአዲስ መልክ ህጋዊ አደረጃጀት ይዞ መቋቋሙን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ማህበሩን ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደረጋል ብለዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ወይዘሮ በረከት ወርቁና ምክትል ፕሬዚዳንቷ ሳራ ሀሰንም ሴት የንግዱ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።
ሴት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አቅምን የሚያጠናክሩ ስራዎችን በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።