ጾሙን በመረዳዳትና ለዘላቂ ሰላም በመስራት ማሳለፍ ይገባል- ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሔም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
ጾሙን በመረዳዳትና ለዘላቂ ሰላም በመስራት ማሳለፍ ይገባል- ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሔም ቱፋ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ጾምን በመረዳዳት እና ለሀገር ዘላቂ ሰላም በመስራት እንዲያሳልፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሔም ቱፋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የዑለማዕ ሶስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ዑለማዕ ጉባኤ ሰብሳቢ ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እና የኢትዮጵያ አሊሞች ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ጀይላን ኸድር(ዶ/ር) ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ዑለማዕዎችና የክልል መጅሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዳሉት ህዝበ ሙስሊም የረመዳን ጾምን ሲያሳልፍ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ዑለማዕዎችም መተጋገዝና መረዳዳት እሴትን ማስተማር ይገባቸዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል በጾም ወቅት ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዑለማዕ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ጀይላን ኸድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለሁለት ቀናት በሚካሔደው ጉባዔ በእስልምና ምክር ቤት ምርጫ አፈፃፀም መመሪያ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ለውጡን ተከትሎ መንግስት የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት እንዲጠናከር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡